About Us

abt-img.jpg
-

የፕሬዚደንቱ መልዕክት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በኾነው፡፡
ውድ እና የተከበራችሁ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ።

ከሁሉ አስቀድሜ የአላህ ሰላም እና እዝነት በእናንተ ላይ ይሁን…አሰላሙዓለይኩም ወራሕመቱሏሂ ወበረካትሁ እላለሁ፡፡

እስልምና በመጨረሻው መልዕከተኛ ነብዩ ሙሐመድ ሰለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም (ሰ.ዓ.ወ) ለሰው ዘር በሙሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበከው በመካ ምድር ነበር፡፡ ከመካ ውጭ እስልምና የረገጣት የመጀመሪያዋ ምድር አገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያዊ ሙስሊምነታችን እስልምና ገና በአንቀልባ ጊዜው ላይ ሳለ ይጀምራል፡፡ በነብዩ ሙሐመድ ሶዓወ ልጅነት፡ እድገት፡ የእስልምና አስተምህሮት፡ መከራ፡ ድሎት፡ እና ሕልፈት ውስጥ ሁሉ ያለፍን ታሪካዊ ህዝቦች ነን፡፡

አትዮጵያዊያን እና እስልምና ትስስራቸው ታሪካዊ ቢሆንም በአገራችን በአራቱም ማዕዘናት ከነበሩት ገናና ኢስላማዊ ግዘቶች እና አስተዳደሮች መክሰም በተለይም ከአፄዎች የክርስትያን ሥርዓቶች መስፋፋት ወዲህ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ተቋማዊ አደረጃጀት አልነበራቸውም፡፡ የአሰከፊ ዘመናቱ የሙስሊሞች ቀዳሚ አጀንዳ ህልውናን ማረጋገጥ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በእምነታቸው ጥላ ስር በአንድነት በመሰባሰብ ተቋም መስርተው መኖር የጀመሩት እግጅ ዘግይቶ ክርስትያናዊ የአፄዎቹ አገዛዝ ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዶ ኢትዮጵያ አገራችን የሁላችንም እኩል አገራችን ከሆነችበት ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ ነው፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባኤ በመባል የሚታወቀው የመጀመሪያው የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ተቋም መጋቢት 4 1968 ዓ.ል በቀደምት አባቶቻችን ከፍተኛ ተጋድሎ በይፋ ተመሰረተ፡፡

እልህ አስጨራሹ የምስረታ ሂደት ፊት አውራሪ የነበሩት ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ (ረሕመቱሏሂ ዓለይህ) የመጀመሪያው ሊቀመንበር በመሆን ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት 1981 ዓ.ል ድረስ ተቋማችን አገልግለዋል፡፡

የሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ህልፈት በኋላ የመጅሊሳችን እጣ ፋንታ አሳዛኝ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ጠንካራ ተቋም በመሆን የተቋቋማበትን ዓላማ ማሳካት ቀርቶ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥቃት ማስፈፀሚያ መሳሪያ ሆነ፡፡ በሂደትም ከኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ጋር ያለው ትስስር እየላላ ሄዶ በርካታ ወገኖች የማያወቁት ተቋም የመሆን ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ እጅግ ብዙ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የተቋም ባለቤት ስለመሆናቸው የሚያውቁበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ መጀሊሱን ቢተወውም መጅሊሱ ግን ሴራ በመጎንጎን ሙስሊሙን አልተወውም፡፡

መጅሊሱ በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ለብዙ ዓመታት ቢቆይም አምባገነኑ የኢህአዴግ አገዛዝ ፍፁም ኢ-ሕገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ ተቋሙን እንደመሳሪያ በመጠቀም በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ ያደረሰው ጥቃት ብሶትን ወለደ፡፡ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በሌላ አገር መሰረቱን ካደረገ ከአንድ የእምነት ቡድን ጋር በማሴር እና ህጋዊ ከለላ በመስጠት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ አንድን አስተሳሰብ በኃይል ለመጫን ሙከራ ተደረገ፡፡ ይህም ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቅሶ የድምፃችን ይሰማ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴን ወለደ፡፡ እንቅስቃሴው ካነሳቸው አንኳር ጥያቄዎች አንዱ የጠንካራ ተቋም ባለቤትነት ጉዳይ ሆነ፡፡ ከ10 ዓመታት ያላሰለሰ ጥረት በኋላ የመጣውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ የተቋም ባለቤትነት ጥያቄያችን በአዋጅ የተደገፈ ምላሽ በማግኘት ሙሉ በሙሉ ተመለሰ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የመላ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የጋራ መንፈሳዊ ጥላ ነው፡፡ የተቋማችን መስራች እና የመጀመሪያው ሊቀመንበር የነበሩት ባለራዕይ መሪ ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ህልማቸው እና ጥረታቸው “አንድ ሥርዓት ባለው ድርጅት እየተመራን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መፈፀም እንዲሁም አገራችንን ኢትዮጵያን በብሔራዊ ስሜት ተሳስረን ማገልገል” ነበር፡፡ ይህ እምነት እኛም በአደራ የምንጠብቀው ጉዳይ ነው፡፡ በአስተሳሰቡ፡ በብሔሩ፡ በቆዳ ቀለሙ፡ በፆታ፡ እና በመሳሰሉ የማንነት መለያዎቹ ተነጥሎ ከጋራ የተቋም ባለቤትነት የሚቀር አንድም ኢትዮጵያዊ ሙስሊም የለም፡፡ የተቋማችን ቀዳሚ አጀንዳ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች አንድነት ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ! ተቋማችንን ሁለት ዓበይት ተግባራት የተቋማችን ባህሪ መገለጫ ናቸው፡፡ አንደኛው እንደ ሙስሊም ህዝቦች መንፈሳዊ ግዴታዎችችን እርስ በርስ የምናሳልጥበት የመስተጋብር ክፍል ነው፡፡ በዚህ ውስጣዊ እንቅስቃሴያችን ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በትግላቸው የመሰረቱት ተቋማቸውን በመጠቀም በሙሉ የባለቤትነት ስሜት በተቋማቸው ይሳተፋሉ፡ ይገለገላሉ፡፡ ተቋማቸውን እንዲያስተዳድሩ አደራ የጣሉባቸውና በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊዎች በተጠያቂነት ስሜት እና ቀና የመተናነስ መንፈስ ማገልገል ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን ያምናሉ፡፡ ተቋማችንን ተጠቅምን እምነታችንን እና ማንነታችንን በነፃነት እንተገብራለን፡ እንጠብቃለን፡ እናጎለብታለን፡ ለቀጣዩ ትውልድም እናስተላልፋለን፡፡

ሁለተኛው ባህሪ እንደ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ህዝቦች ከአገራችን መንግስት፡ በየደረጃው ካሉ የመንግስት ተቋማት፡ መንፈሳዊ እና መንፋሳዊ ካልሆኑ ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፡ ታዋቂ ግለሰቦች እና መሰል አካላት ጋር የሚኖረን የሁለትዮሽ የስራ ግንኙነቶችን የምናሳልጥበት መስተጋብር ነው፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በፌዴራል ደረጃ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሁሉ ላዕላይ ወካይ እና ተጠሪ ተቋም ነው፡፡ አዋጃዊ መሰረቱም የፀና ነው፡፡ በመሆኑም መጅሊሳችን ከላይ በስም ከተጠቀሱ አገራዊ እና የባህር ማዶ ህጋዊ አካላት ጋር በሁለቱም የስራ መድረኮች ለኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መንፈሳዊ እና ልማታዊ ጥቅሞች መጠበቅ እና ተጠቃሚነት በትብብር ይሰራል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ! ተቋማችን አንፃራዊ የለጋ እድሜ ባለቤት ነው፡፡ ምንም እንኳን እንደ መንፈሳዊ ማህበረሰብ ታሪካዊ ብንሆንም፡ ዘመናዊ ተቋም መስረተን መንቀሳቀስ ከጀመርን ጥቂት ዓሰርት ዓመታትን ነው ያሰቆጠርነው፡፡ የኢትዮጵያን ግማሽ ህዝብ ያፈቀ ተቋም ባለቤት ብንሆንም የብዛታችንን ግዘፈት የሚመጥን ተቋማዊ አደረጃጀት እና አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ ስራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡ በመሆኑም ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ያላሰለሰ አስተዋፅኦዋችሁን ትለግሱ ዘንድ የከበረ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡ ከወረዳ እስከ ክልል እና ፌዴራል ደረጃ ድረስ የተዘረጋው ሰፊ የአስተዳደር መዋቅር ሁሉ አቀፍ ተሳትፎን ይፈልጋል፡፡ ያለ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የነቃ ተሳትፎ በጋራ የተለምናቸውን ህልሞች ማሳካት እንደማይቻል ከእናንተ ወገኖቼ የተሰወረ አይደለም፡፡ እንደ የተቋማችን መሪ ይህንኑ ለማስታወስ ስሞክር ከፀና አደራዬም ጭምር ነው፡፡

EIASC Copyright© 2022